ማኅበራዊ ስነ-ልቦናዊ ድጋፍ ለጤናማ ቤተሰብ

ማስታወሻ፡ የባለታሪኮቹን ስሜት ለመጠበቅ ስማቸው ተቀይሯል።

ኦገስት 24, 2022

ማኅበራዊ ስነ-ልቦናዊ ድጋፍ  ለጤናማ ቤተሰብ Banner Image

ኤደን ውልደቷና እድገቷ በአዲስ አበባ ከተማ የሆነ ታዳጊ ወጣት ናት። ኤደን እና ሦስቱ ታናናሽ እህቶቿን በብቸኝነት ያሳደገቻቸው ታታሪዋ እናታቸው ከበቡሽ ናት። ከበቡሽ ለቤተሰቧ የሚያስፈልገውን ለማሟላት በተሰማራችበት የችርቻሮ ንግድ ጠንክራ ብትሰራም ኑሯቸው በአብዛኛው ከእጅ ወደ አፍ ነበር። የከበቡሽ ገቢ መሠረታዊ ፍላጎቶችን እንኳን ለማሟላት የሚበቃ ስላልነበረ ዕለት ዕለት ቤተሰቡን የሚያሳስብ ጉዳይ ሆኖ ቆየ። የኤደንን ቤተሰብ አሳሳቢ ሁኔታ በቅርበት የሚያውቀው የሚመለከተው የመንግስት አካል ቤተሰቡ በቤታኒ የቤተሰብ ጥበቃ እና አቅም ማጎልበት መርኃ ግብር እንዲቀላቀሉ አድረገ።

የኤደን ቤተሰብ ከቤተሰብ ጥበቃ እና አቅም ማጎልበት መርኃ ግብሩ የሚያገኙት የስነ-ምግብ፣ የሕክምና፣ የትምሕርት እንዲሁም የሌሎች አገልግሎቶች ኑሮአቸው መሻሻል ጀመረ። በተጨማሪም፣ የኤደን ቤተሰብ የልጆች አስተዳደግ እና የህይወት ክሂሎት ስልጠናን ማግኘት ችለዋል። ሆኖም ነገሮች መሻሻል ሲጀምሩና ቤተሰቡ በተረጋጋ ኑሮ ውስጥ ሆነው፣ ከበቡሽ ከገጠማት አጣዳፊ ጉዳይ የተነሳ ከአዲስ አበባ ውጪ ተጓዘች። ያን ጊዜ፣ ኤደን የሦስት እህቶቿ አሳዳጊ የመሆን ኃላፊነት ገጠማት።

ከበቡሽ ባሰበችው ፍጥነት ወደ አዲስ አበባ ለመመለስ አልቻለችም። በዚህም ምክንያት፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን የምትከታተለው ኤደን ምግብ ማብሰል፣ ልብሶችን ማጠብ፣ ቤት ማጽዳት፣ የእህቶቿን ንጽህና መጠበቅ እንዲሁም ትምህርታቸውን ማስጠናት ግዴታዋ ሆኖ ቆየ። ባለ ብሩህ አዕምሮዋ ኤደን ለእርሷና ለእህቶቿ የዕለት ጉርሳቸውን በማግኘት ስለ ተጠመደች ትምህርቷን እንደሚገባ ለመከታተል አልቻለችም። በመሆኑም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ማጠናቀቂያ ፈተናዋን ለማለፍ የሚያስችል በቂ ውጤት ለማምጣት ሳትችል ቀርታ ወደ ዩኒቨርስቲ ለመግባት አልቻለችም። ኤደን ወደ ዩኒቨርስቲ ለመግባት፣ ተምሮ ለመመረቅ እና መጠነኛ ገቢ አግኝታ እናቷን ለመደገፍ የነበራት ህልም ተጨናገፈ። መሬት የከዳት፣ ተስፋዋ የጨለመባት መስሎ ተሰማት። ያን ጊዜ፣ ራሷን የማጥፋት ሀሳብ ይመላለስባት ጀመር።

የቤታኒ የቤተሰብ ጥበቃ እና አቅም ማጎልበት መርኃ ግብር አንድ አካል በሆነው የቤተሰብ ጉብኝት ወቅት የኤደንን ቤተሰብ የጎበኘው የማኀበራዊ ጉዳይ ባለሙያ ኤደን ከነበረችበት ድባቴና ተስፋ መቁረጥ ለመውጣት ማኅበራዊና ስነ-ልቦናዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋት ተረዳ። ኤደንም ድጋፉን ለማግኘትና ከአስር የሚበልጡ የምክክር ጊዜያትን ለመከታተል ፈቃደኛ ሆነች። በምክክር ክፍለ ጊዜው ወቅት፣ ኤደን ስለ ሕይወት አዲስ አመለካከትን ለማዳበር፣ ውጥረትን ለመቋቋም የሚያስችሉ ስልቶችን ለመማር ቻለች። የምክክር ጊዜያቱ በተካሄደበት ወቅት ሁሉ፣ ስለ ማንነቷ እና ስላላት እምቅ አቅም ትክክለኛ ግንዛቤን አገኘች። በክፍለ ጊዜያቱ ለሕይወት ያላትን ትርጉም መልሳ እንድታጤን የሚያስችሉ ከህሎቶችን አግኝታለች። አሁን ላይ ኤደን ያገኘችውን አዲስ እውቀት በመጠቀም፣ የቤተሰቧን ኑሮ ለመደጎም እና የግል ኮሌጅ ገብቶ ትምህርት ለመማር የሚያስችላትን ገንዘብ የምታገኝበትን አነስተኛ የንግድ ሥራ ጀምራለች። የራሷን ሕይወት በመምራት እና ቤተሰቧን በማገዝ መካከል ያለውን ጤናማ ሚዛን ጠንቅቃ አውቃለች። ሕይወቷን በተረጋጋ መንገድ ለመምራት እና ግቧን ለማሳካት የሚያስችላትን አቅም ከተሰጣት ማህበራዊና ስነ፟ልቦናዊ አገልግሎት አግኝታለች።